Logo

ከዘማሪ በረከት ለማ ጋር ያደረግነው ቆይታ

By Gelila AdamuMarch 3rd, 2025

ከምንወደው የጌታ ባርያ ዘማሪ በረከት ለማ ጋር ደስ የሚል ቆይታ አድርገናል።
ያቦቅን ስሻገር, አንተን ባየ አይኔ, ትሁን ፈቃድህ እና በሌሎችም ዝማሬዎች ከባረከን ወጣቱ ዘማሪ
በረከት ለማ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንድትከታተሉ ጋበዝናችሁ።

ጥያቄ፦ ዝማሬ አገልግሎት ውስጥ እንዴት ገባህ?

በረከት፦
"በልጅነቴ ከ Sunday school እንደጨረስኩኝ የተቀላቀልኩበት የመጀመሪያው ህብረት ኳየር ነበረ። በተጨማሪ ባደኩባት ሕይወት ብርሃን ቤ.ክ የአምልኮ አገልግሎት ውስጥም ገብቼ ስለነበር ለዝማሬ አገልግሎት ቅርብ ነበርኩኝ። በዚህ ሁኔታ ነው ወደ ዝማሬ አገልግሎት የገባውት።"

ጥያቄ፦ አገልግሎት ላንተ ምንድነው?

በረከት፦
"አገልግሎት ማለት በተገልጋዩና በአገልጋዩ መካከል ያለ ቁርኝት ነው። ማንም ሰው ታማኝ ተደርጎ በተሾመበት በየትኛውም ቦታ ለሚያገለግለው ጌታ ደስታ መኖር ሲጀምርና ተገልጋዩ ጌታ በአገልግሎቱ ሲደሰት ትክክለኛ አገልግሎት ነው ብዬ አምናለሁ።"

ጥያቄ፦ ግቢ ስለነበረህ ቆይታ እና ከጊቢ ህይወት ጌታ ምን አስተማረህ?

በረከት፦
"ለአንድ ክርስቲያን ግቢ ሲባል ከትምህርቱ ባሻገር ቀድሞ ወደ አእምሮ የሚመጣው ነገር Fellowship ነው። በግቢ ውስጥ በነበረኝ ቆይታ በ Evangelism, Choir እንዲሁም በ Main leadership ላይ የማገልገል እድል አግኝቼ ነበር። ግቢ በነበርኩ ጊዜ ከጌታ የተማርኳቸው ለህይወት የሚሆኑ ትምህርቶችና ንክኪዎች ነበሩኝ።"

"መቅደም ቀድሞ በመሮጥ አይደለም ለእግዚአብሔር በመሸነፍ ነው ፤ ያዕቆብ ሮጦ ሄዶ ያታለለ ጊዜ ሳይሆን ሹሉዳውን ተነክቶ ተሸንፎ ያነከሰ ቀን ነው የቀደመው"
— በረከት ለማ

ጥያቄ፦ "ያቦቅን ስሻገር" የሚለውን ዝማሬ ስትቀበል ምንድነው የገባህ?

በረከት፦
"በአንድ ወቅት በራሴ ጥረትና ጥበብ ነገሮችን ለማስኬድ ሞክሬ ያልተሳካልኝ ጊዜ ነበር። በዚህም ምክንያት ቀና ለማለትና ለመፅናናት ትንሽ ጊዜ ወሰደብኝ። ጌታ ግን በእነዚያ ቀናት ከያዕቆብ ህይወት ያስተምረኝ ነበር እንደውም በዚያን ሰሞን በቃሉ ሲያፅናናኝ ውስጤ ከቀሩ ድምጾች መካከል አንዱ "መቅደም ቀድሞ በመሮጥ አይደለም ለእግዚአብሔር በመሸነፍ ነው ፤ ያዕቆብ ሮጦ ሄዶ ያታለለ ጊዜ ሳይሆን ሹሉዳውን ተነክቶ ተሸንፎ ያነከሰ ቀን ነው የቀደመው" የሚለውን እስከዛሬ አልረሳውም። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ጌታ ይህን ዝማሬ ሰጠኝ።"

ጥያቄ፦ እንዴት ነው የመጀመሪያውን መዝሙር የተቀበልከው?

በረከት፦
"የመጀመሪያ መዝሙሬን አላስታውሰውም ነገር ግን በምጸልይበት ሰዓት ጌታ ዝማሬዎችን ወደ ልቤ ያፈሳቸዋል። ጌታ ስለሰጠኝ ቃል አሰላስላለሁ ፣ ጸልያለሁ ፣ ከወዳጆቼ ጋር አወራለሁ ከዚያን ከጊዜያት በኋላ ወደ ዝማሬ ይለወጣል።"

ጥያቄ፦ እንደ ምሳሌ የሆነልህና እራስህን እንድታሳድግ የረዳህ ሰው ካለ ልትነግረን ትችላለህ?

በረከት፦
"ጌታዬ ኢየሱስ ከበራልኝ ወዲህ ስለ ጌታ ማጥናት እሱን ለመምሰል መፈለግ በውስጤ ያድር ስለነበር ትልቁ ምሳሌዬ ኢየሱስ ነው። በመቀጠል ግን አርዓያ በመሆን በተለያየ መንገድና ሁኔታ ህይወቴ ላይ ተጽዕኖ የፈጠሩ በርካታ ሰዎች አሉ።"

ስለሰጠኸን ውድ ጊዜህ ተባረክልን ቤኪ። በሌላ አልበም አና አገልግሎት እንድትባርከን ጌታ ፀጋውን ያብዛልህ። ወጣትነትን ለጌታ መስጠት ትልቅ ክብር እንደሆነ ማሳያ ነህና ቀሪውም ዘመንህ በቤቱ ይለቅ።


@Zemareapp የምትከታተሉ ቤተሰቦቻችን ከቤኪ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደወደዳችሁት ባለ ሙሉ ተስፋ ነን።

በመጨረሻም 'አንተን ባየ አይኔ' ከተሰኘው የቤኪ መዝሙር በጣም የሚማርከንን ስንኝ እንጋብዛቹህ።
ይሁና የኔ ሳቅ (ይሳቅ) ለሱ
ይሁና ደስታዬ ለሱ
ይበሉኝ ባዶ የቀረ
ይበሉኝ የተሞኘ