ከዘማሪት እየሩሳሌም (ጄሪ) ጋር ያደረግነው ቆይታ
ሰላም የተወደዳችሁ ቤተሰቦቻችን እንዴት ናችሁ። ዛሬ ደግሞ በጥያቅያችሁ መሰረት የዘማሪት እየሩሳሌም ነጊያን ምላሽ ይዘንላችሁ መተናል።
ዘማሪት እየሩሳሌም (ጄሪ) እጅግ የተወደደች በአገልግሎቷ ብዙ የተባረክንባት የእግዚአብሔር ባሪያ ናት። በርከት ያሉ ዝማሬዎችን የሰጠችን ጄሪ ካዜመቻቸው ዝማሬዎች መካከል አውቃለሁ፣ ፍቅሩ አያረጅም፣ አለኝታዬ፣ የዜማ ጊዜ እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ።
እንደተለመደው ከእናንተው ከኢንስትግራም ቤተሰቦቻችን ለዘማሪት እየሩሳሌም ነጊያ (ጄሪ) ላቀረባችሁላት ጥያቄዎች ምላሾቿን ከዚህ በታች ያገኙታል።
ጥያቄ፦ ጌታ በምን አይነት ሁኔታ ነው ያገኘሽ? ወደ ኋላ መለስ ብለሽ ብታጫውቺን።
እየሩሳሌም (ጄሪ):- በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ ነው ያደኩት። በግሌ ጌታን ለመከተል የወሰንኩት ግን የሶስተኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ ነበር።
ጥያቄ፦ እንደሰው አይደለም የሚለውን መዝሙር እንዴት ተቀበልሽው?
እየሩሳሌም (ጄሪ):- በአንድ ወቅት እራሴን ከባድ የሆነ ችግር ውስጥ አገኘሁት። እናም ለሚቀርበኝ ሰው የገጠመኝን ነገር በማማክርበት ወቅት የጠበኩትን ምላሽ አላገኘሁበትም። ነገር ግን ከእግዚአብሔር ጋር በመነጋገርና ምህረት ቸርነቱን በማሰብ ይቅርታ የተደረገልኝ ሰው መሆኔንና የእግዘብሔርን ያልተለወጠ አብሮነትና ያልቀዘቀዘ ፍቅር ሊሰማኝ በመቻሉ ነው ይህን ዝማሬ (እንደ ሰው አይደለም) ልፅፈው የቻልኩት።
ጥያቄ፦ በጌታ ቤት ለማገልገል ትልቁ ቁልፍ ነገር ምንድን ነው?
እየሩሳሌም (ጄሪ):- ቁልፉ ነገር የጠራንን ማወቅና ማክበር ነው ብዬ አምናለሁ። 1 ጢሞ 1÷12 መፅሀፍ ቅዱስ ሲናገር ታማኝ አርጎ ስለቆጠረኝ ለአገልግሎቱ ሾመኝ ይላል። ሌላው እግዚአብሔር በኛ እንደሚሰራ አምነን በፅናት ማገልገል ቁልፍ ነገር ነው ብዬ አምናለሁ።
ጥያቄ፦ እንደ ሰው በመንፈሳዊ ህይወትሽ ስትደክሚ የሚያበረታሽ ነገር ምንድን ነው?
እየሩሳሌም (ጄሪ):- በህይወቴ ስደክም ጌታ እየሱስ በመስቀል ላይ የከፈለልኝን ዋጋና ፍቅሩን ሳስብ ከነበርኩበት ድካም ወጥቼ ወደ ንስሀ መንፈስ እገባለሁ። ለንሰሃና መንፈሳዊ ህይወትን የሚያነቃቁ ዝማሬዎችና ስብከቶችን እሰማለሁ።
ጥያቄ፦ አሁን ለሚመጡ አዳዲስ ዘማሪዎች ምን ትመክሪያለሽ?
እየሩሳሌም (ጄሪ):- ለአዳዲስ ዘማሪዎች የምመክረው የእግዚአብሔርን የልብ ፍቃድ በማገልገል ላይ እንትጋ ነው። ሌላው ደግሞ ትሁት መሳዬች ሳይሆን የእውነት ትሁታን እንሁን። ቅዱስ ቃሉ ለትሁታን ፀጋን ይጨምራል ይላል። ስለዚህ ፀጋ እንዲጨመርልንና አገልግሎታችን ሞገስ እንዲኖረው ትሁታን እንሁን።
ጥያቄ፦ አዲስ አልበም መች እንጠብቅ
እየሩሳሌም (ጄሪ):- አልበም ለማውጣት እንቅስቃሴ ጀምሪያለሁ። መቼ እንደሚወጣ ግን እርግጠኛ መሆን አልችልም። አልበም ለመስራት በዝግጅት ላይ እገኛለሁ።
የተወደዳችሁ ቤተሰቦቻችን ከዘማሪት ጄሪ ጋር የነበረን ቆይታ ይህን ይመስላል። በብዙ እንደተማራችሁበት ተስፋ እናደርጋለን። ጄሪም ስለሰጠሽን ጊዜ እናመሰግናለን። እግዚአብሔር ፀጋውን ጨምሮልሽ በአዳዲስ ዝማሬዎችሽ እንደምንባረክ ባለ ሙሉ ተስፋ ነን።
እንደተለመደው እጅግ ከተወደደው የዛሬው እንግዳችን ዝማሬ ውስጥ 'ገነቴ ነህ' ከሚለው ዝማሬ የተማረክንበትን ግጥም በመጋበዝ እንሰናበታለን።
ባልበላም ጠግቤ አድራለው
ባልጠጣም እረክቼ እኖራለው
አንተ ካለህ ምን እሆናለው?
አንተ ካለህ ምን እሆናለው?
በረሀው ላይ አስቀኸኛል
ገነቴ ነህ አርክተኸኛል
ፍቅርህ ብቻ ይበቃኛል
መገኝትህ ያረካኛል
አንተ ካለህ ምን ያሻኛል
ፊትህ ብቻ ይበቃኛል።