ከዘማሪት ህሊና ካሳሁን ጋር ያደረግነው ቆይታ
ዘማሪት ህሊና ካሳሁንን ጠይቁልን ባላችሁን መሰረት ምላሾቿን ይዘንላችሁ ቀርበናል። አብራችሁን ቆዩ
ጥያቄ፦ ዝማሬ ላንቺ ምንድን ነው?
ህሊና፦
"ዝማሬ ማለት በኔና በጌታ መካከል ያለ የፍቅር ቋንቋ ነው። እኔ ለእግዚአብሔር ያለኝን ፍቅር የምገልፅበት መንገድ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ዝማሬ መንፈሳዊ የጦር መሳሪያ ነው። የእግዚአብሔርን ሃይል በታጠቁ ዝማሬዎች ነፍሳት ነፃ ይወጣሉ፤ ከእስራት ይፈታሉ።"
ጥያቄ፦ መዝሙሮችን ከእግዚአብሔር የምትቀበዪው በምን አይነት መንገድ ነው?
ህሊና፦
"ጌታ እየሱስ ነው ዝማሬዎችን በልቤ የሚያስቀምጠው። ብዙ ጊዜ ዝማሬዎቼ መነፈስ ቅዱስ በልቤ ከሚያስቀምጠው ሃሳብና ማንነቴን ከነካኝ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የመነጩ ናቸው። ዝማሬዎቼ በሙሉ በመንፈስ ቅዱስ የተፀነሱ እንጂ የአማርኛ ቋነቋ ስነ-ግጥም ክህሎትና የሙዚቃ እውቀት ኖሮኝ አይደለም የሰራኋቸው።"
"እውነተኛው ለእግዚአብሔር የሚቀርብ አምልኮ በመንፈስ ቅዱስ ፅንሰት መሆን አለበት ብዬ ነው የማምነው።"
— ህሊና ካሳሁን
ጥያቄ፦ ጌታን ያገኘሽበትን አጋጣሚ አስታውሺን
ህሊና፦
"አንድ አጋጣሚ አለኝ ብዬ መናገር አልችልም። ብዙ አጋጣሚዎች አሉ፤ ወደፊትም ይኖራሉ። እግዚአብሔርን በሙሉ ልባችን ስንፈልገውና ከሱ ጋር እውነተኛ ግንኙነት ሲኖረን በጌታ እንነካለን። ከቤተሰቤ ጋር ጌታን ከተቀበልን ጀምሮ (በ7 አመቴ) መንፈስ ቅዱስ እራሱን እንደሰው ነበር ያስተዋወቀኝ።"
ጥያቄ፦ የእግዚአብሔርን ድምፅ መስማት የምንችለው እንዴት ነው?
ህሊና፦
"የእግዚአብሔርን ቃል የምንሰማበት ዋነኛው መንገድ የእግዚአብሔርን ቃል በማንበብ ነው። በመንፈስ ቅዱስ ታግዞ የእግዚአብሔርን ቃል ማንበብና ማሰላሰል የእግዞብሔርን ድምፅ መስማትን እንድንለማመድ ይረዳናል።"
ጥያቄ፦ በጣም የምትወጂውን መዝሙር እና ዘማሪ ንገሪን?
ህሊና፦
"በብዙ የተባረኩባቸው ዘማሪዎች ፀሎት ስዩም፣ ሊሊ ጥላሁን፣ ዳጊ ጥላሁን፣ ፓ/ር ተስፋዬ ጋቢሶ፣ ሀይሌ ጫላ፣ ቤቲ ተዘራ እና የመሳሰሉት ናቸው። ከእየሱስ ጋር ያለንን ቅርበት የሚሰብኩ ዝማሬዎች በይበልጥ ይማርኩኛል።"
ዘማሪት ህሊና ስለሰጠሽን ጊዜ እግዚአብሔር ይባርክሽ። በ @Zemareapp ቤተሰቦች ስም እግዚአብሔር ዘመንሽንና አገልግሎትሽን ይባርክ።