ከዘማሪ እላሻ ፍቃዱ ጋር ያደረግነው ቆይታ
ከምንወደው የጌታ ባርያ ዘማሪ እላሻ ፍቃዱ ጋር ደስ የሚል ቆይታ አድርገናል።
እላሻ ፍቃዱ እንደገና፤ ስላንተ በሚሉት የዝማሬ አልበሞች እና በርከት ያሉ ሙዚቃዎችን በማቀናበር ይታወቃል።
ወጣቱ እጆቹን ካሳረፈባቸው መዝሙሮች መካከል የተወዳጇ ዘማሪት ዘሪቱ ከበደ መዝሙሮች ከብዙ በጥቂቱ ይጠቀሳል።
ከናንተው ከቤተሰቦቻችን ለቀረቡለት ጥያቄዎች እላሻ ተከታዩን ምላሽ ሰቶበታል።
ጥያቄ፦ ጌታን እንዴት ተቀበልክ?
እላሻ፦
"ጌታን በሚያውቅ ቤተሰብ ውስጥ ነው ተወልጄ ያደግሁት:: ያ ጥሩ መደላድል ፈጥሮልኛል:: ካደግሁ በኇላ ደግሞ ጌታ በራሱ መንገድ ራሱን ገልጦልኛል::"
ጥያቄ፦ ዝማሬ ላንተ ምንድን ነው?
እላሻ፦
"ዝማሬ ለእኔ ስጦታ እና ጥሪ ነው::"
ጥያቄ፦ የእግዚአብሔርን መገለጥ በህይወትና አገልግሎትህ ላይ እንዴት ተረዳህ?
እላሻ፦
"ሁሉን የምረዳው በአባትነት ፍቅሩ ውስጥ ነው:: እግዚአብሄር ራሱን የገለጠው በክርስቶስ ነው:: ይህ በአገልግሎትም ይሁን በግል ህይወት የተለያየ ሆኖ አይታየኝም::"
ጥያቄ፦ የመዝሙሮችህን ግጥም እንዴት ነው ምትፅፋቸው?
እላሻ፦
"መዝሙር ለመጻፍ ብዬ አልጽፍም:: ከተመስጦ ውስጥ ነው የምጽፋቸው:: ከዚህ ምንም የተለየ ሌላ የአጻጻፍ መንገድ የለኝም::"
ጥያቄ፦ እንዴት ነው የመጀመሪያውን መዝሙር የተቀበልከው?
እላሻ፦
"የመጀመሪያ መዝሙሬን አላስታውሰውም ነገር ግን በምጸልይበት ሰዓት ጌታ ዝማሬዎችን ወደ ልቤ ያፈሳቸዋል። ጌታ ስለሰጠኝ ቃል አሰላስላለሁ ፣ ጸልያለሁ ፣ ከወዳጆቼ ጋር አወራለሁ ከዚያን ከጊዜያት በኋላ ወደ ዝማሬ ይለወጣል።"
ጥያቄ፦ ስምህ ለየት ያለ ነው። ትርጉሙን ማወቅ ከተቻለ...
እላሻ፦
"እናቴ ቤት ውስጥ እኔን የምትጠራበት ስም ነበር:: ከእርሷ ማረፍ በኇላ ለርሷ ማስታወሻነት ወደህጋዊነት መጥቶ ነው።"
ስለሰጠኸን ውድ ጊዜህ ተባረክልን እላሻ። በሌላ አልበም አና አገልግሎት እንድትባርከን ጌታ ፀጋውን ያብዛልህ። ወጣትነትን ለጌታ መስጠት ትልቅ ክብር እንደሆነ ማሳያ ነህና ቀሪውም ዘመንህ በቤቱ ይለቅ።
@Zemareapp የምትከታተሉ ቤተሰቦቻችን ከእላሻ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደወደዳችሁት ባለ ሙሉ ተስፋ ነን።
በመጨረሻም 'ህይወት ሆኖልኛል' ከተሰኘው የእላሻ መዝሙር በጣም የሚማርከንን ስንኝ እንጋብዛቹህ።
ባርያ ሆኜ ሳለሁ
የኃጢአት ባለዕዳ
ሰይጣን አሸክሞኝ
የዘመን አበሳ
ነገር ግን ነፃነትህ
በሬን ከፍቶ ገባ
በተራ አይደለም
በዘለዓለም ጌታ
ህይወት ሆኖልኛል
ነፃ አውጥቶኛል
ለእኔ ሞቷልና
አቀርባለሁ አምልኮ ምስጋና