ከፓስተር ተከስተ ጌትነት ጋር የነበረን ቆይታ
ፓስተር ተከስተ ጌትነትን ጠይቁልን ባላችሁን መሰረት የፓስተር ተከስተ ጌትነትን መልሶች ይዘንላችሁ መጥተናል። አብራችሁን ሁኑ!
ጥያቄ፦ ጌታን እንዴት አገኘህ?
ፓስተር ተከስተ ጌትነት፦
"ከረጅም አመታት በፊት አንድ አሜሪካዊ ከጎዳና አንስቶ በወቅቱ የተሃድሶ ህብረት ከሚባል የክርስቲያን ህብረት ጋር የመገናኘት እድሉን አገኘሁ። በጊዜ ሂደትም ጌታ እየሱስን በሙላት ማምለክና ህብረት ማድረግ ብሎም በዝማሬ ማገልገል ጀመርኩ።"
ጥያቄ፦ የክርስትና ከባዱ ፈተና ምንድን ነው?
ፓስተር ተከስተ ጌትነት፦
"እንደ ቃሉ አለመኖር ከባዱ ፈተና ነው። እኛ ሰዎች አርነት ከሆነልን በኋላ በክርስትና ውስጥ ለውጥ፣ በረከትና ረድኤት ያለው ህይወት የሚኖረን እንደ እግዚአብሔር ቃል መኖር ስንችል ነው። ይህ ከባዱ የክርስትና ፈተና ነው።"
"ትክክለኛውን የክርስቶስን መረዳት ማግኘት ሚቻለው ሰዎችና አገልጋዮች ስለ እግዚአብሔር ባብራሩልን ልክ (Frame) ሳይሆን በግል መፅሐፍ ቅዱስን በማንበብ ነው።"
— ፓስተር ተከስተ ጌትነት
ጥያቄ፦ መዝሙሮችን እንዴት ነው ከጌታ የምትቀበለው?
ፓስተር ተከስተ ጌትነት፦
"በኔ ልምድ መዝሙር ፀጋ፣ ስጦታና ከእግዚአብሔር የሚሰጥ እንደሆነ ነው ማምነው። ስለ እግዚአብሔር ማሰብ ለኔ በቂ ነው። መዝ 77÷3 ላይ መዝሙረኛው ዳዊት እንደተናገረው 'እግዚአብሔርን አሰብኩት ደስም አለኝ' ይላል። በሌላ የቃል ክፍል ላይ ደግሞ 'ደስ ያለው ይዘምር' ይላል። ይህ ለኔ መዝሙርን ከጌታ ምቀበልበት መንገድ ነው።"
ጥያቄ፦ የምንጊዜውም ምርጡ መዝሙር ላንተ የቱ ነው?
ፓስተር ተከስተ ጌትነት፦
"ብዙ የምወዳቸው መዝሙሮች አሉ። በድምፅ ከለር፣ በቃላት አሰካክ፣ እንዲሁም በሚያነሱት ሀሳብ የብዙ ዘማሪዎችን መዝሙሮች እወዳለሁ። ከራሴ መዝሙሮች የቱን የበለጠ እንደምወድ ለመምረጥ ያስቸግራል። እያንዳንዱ መዝሙር የየራሱ ገጠመኝና ሁኔታ ስላለው አንድ መዝሙር መምረጥ ያስቸግራል። እናም ብዙ ናቸው።"
ጥያቄ፦ ዘማሪ የመሆን ከባዱ ፈተና ምንድን ነው?
ፓስተር ተከስተ ጌትነት፦
"በድሮ ጊዜ የዝማሬ ፀጋ እንዲገለጥ የግድ በቤተክርስቲያን ውስጥ የመድረክ እድል ማግኘት ነበረብን። አሁን ላይ ግን የማህበራዊ ሚዲያ መኖር አገልግሎቱን ምቹ አድርጎታል። ሌላኛው ፈተና ደግሞ ከገንዘብ ጋር የተያያዘ ነው።"
ጥያቄ፦ አዲስ አልበም መች እንጠብቅ?
ፓስተር ተከስተ ጌትነት፦
"7ኛ ቁጥር አልበም በ7ኛ ዓመት በሚል እቅድ ቀጣዩን አልበሜን ቀጣይ ዓመት ለመልቀቅ በዝግጅት ላይ ነኝ። 6ኛው አልበሜ ከወጣ 6 ዓመት ሊሆነው ነው። ብዙ ያለቁ መዝሙሮች በእጄ ላይ አሉ፣ ጥቂት የማስተካከያ እና የስቱዲዮ ስራዎች ብቻ ይቀራሉ።"
እኛም በ@Zemareapp ስም እግዚአብሔር ፀጋውን ያብዛልህ። በ7ኛው አልበምህም በብዙ እንደምንባረክበት እናምናለን። ስለሰጠኸን ጊዜ ጌታ ይባርክህ።