Logo

ከዘማሪት ሶሬቲ ሞገስ ጋር ያደረግነው ቆይታ

By Gelila AdamuMay 19, 2025

ሰላም በጌታ የተወደዳችሁ ዛሬ ደሞ ለናንተ ይዘንላችሁ የመጣነው እንግዳ ወጣቷን ዘማሪት ሶሬቲን ነው።

መሉ ስሟ ሶሬቲ ሞገስ ይባላል። በለጋ እድሜዋ ነበር የጌታን ቤት በልጆች ኳየር አያገለገለች ያደገችው። የዝማሬ አገልግሎቷ ከሰንደይ ስኩል የልጆች ኳየር አገልግሎት ጀምሮ በቁጥር ትንሽ የማይባሉ መዝሙሮችን እስከመልቀቅ የዘለቀ እንደሆነም አጫውታናለች።

ዘማሪት ሶሬቲ ካዜመቻቸው ዝማሬዎች ውስጥ አየራራህልኝ፣ መፃተኛ እና ካሰነበትከኝ ይጠቀሳሉ። ዘማሪት ሶሬት ከናንተው ከኢንስትግራም ቤተሰቦቻችን ለቀረቡላት ጥያቄዎች የሰጠችውን ምላሽ ይዘንላችሁ መተናል። አብራችሁን ሁኑ።

ጥያቄ፦ እንዴት ወደ ዝማሬ መጣሽ?

ሶሬቲ፦
"በልጅነቴ በሰንደይ ስኩል የኳየር አገልግሎት ነው ዝማሬ የጀመርኩት። መዘመርም መዝሙር መፃፍም የጀመርኩት በኳየር ውስጥ ነው።"

ጥያቄ፦ የመጀመሪያ መዝሙርሽ ምንድን ነው? ስትቀበይውስ ምን ተለማማመድሽ (Experience) አደረግሽ?

ሶሬቲ፦
"የመጀመሪያ መዝሙሬ ለኳየር ነው የተሰጠው። ከእግዚአብሔር ቃል ቀጥታ ስለተወሰደ ቆንጆ ዝማሬ ነው። ከዘፀአት ምዕራፍ 15 ቀጥታ የተወሰደ የሙሴ እህት ማሪያም የዘመረች መዝሙር ነው።"

ጥያቄ፦ ፀጋውን ያላወቀ ሰው ምን ማድረግ አለበት?

ሶሬቲ፦
"ፀጋውን ያላወቀ ሰው ፀጋ ሰጪውን እግዘብሔርን መጠየቅ ነው ያለበት።"

"ዘማሪ መሆን ከሙዚቃ ታለንት ባለፈ ከእግዚአብሔር ጋር ህብረት ማድረግንና ቅዱስ ቃሉን ማሰላሰልን ይጠይቃል።"
— ሶሬቲ ሞገስ

ጥያቄ፦ የሙዚቃ ታለነት መኖርና ዘማሪ መሆን ልዩነቱ ምንደንነው?

ሶሬቲ፦
"የሙዚቃ ታለነት መኖርና ዘማሪ መሆን ብዙ ልዩነት አለው። የሙዚቃ ታለነት ኖሮት ረብ ለሌለው ነገር ሊተጋና ራሱን ሊሰጥ ይችላል። የሙዚቃ ታለንት ዘማሪ ለመሆን አስፈላጊ ቢሆንም ዘማሪ መሆን ከታለነት ያለፈ ነገርን ይፈልጋል። ዘማሪ መሆን ከሙዚቃ ታለንት ባለፈ ከእግዚአብሔር ጋር ህብረት ማድረግንና ቅዱስ ቃሉን ማሰላሰልን ይጠይቃል።"

ጥያቄ፦ እንደ ዘማሪ በዚህ ዘመን ያለው የአምልኮ ስርአት እውነተኛውን መስዋዕት ለእግዚአብሔር የሚያቀርብ ነው ብለሽ ታስቢያለሽ?

ሶሬቲ፦
"አምልኮ ከዝማሬ የዘለለ ነገር ነው። የዕለት ተዕለት ህይወታችንና መውጣት መግባታችን በራሱ ለእግዚአብሔር የሚቀርብ መስዋዕት ነው። አሁን ላይ ያለው የክርስትና ህይወታችን እግዚአብሔርን የሚያስከብር ነው ለማለት ይከብደኛል። ነገር ግን እግዚአብሔር ተሀድሶን እንደሚያመጣ ተስፋ አደርጋለሁ።"

ጥያቄ፦ የሶሬቲን 3 ጠንካራ ጎኖች ንገሪን?

ሶሬቲ፦
"ቀላል ጥያቄ ባይሆንም የመጀመሪያው ያላመንኩበትን ነገር አላደርግም። ሌላው ስዓት አክባሪ ነኝ ብዬ አስባለሁ። ሶስተኛው የሰው ልጅ በሰውነቱ አከብራለሁ።"

ጥያቄ፦ በዚህ ዘመን ስለሚስተዋለው ቅይጥነት ያለሽ እይታ ምንድነው? ቅይጥነት በቤተ ክርስቲያን አለ? ካለ መገለጫዎቹ ምንድን ናቸው? መፍትሄውስ?

ሶሬቲ፦
"ቅይጥነት በቤተክርስቲያን ውስጥ በሚያሳዝን ሁኔታ በደንብ አለ። መገለጫዎቹ የክርስቶስ መሻት ያልሆኑትን ነገሮች ማስቀደም አልፎም ዋና መድረግ፤ አለማዊነት፤ ሰውን መናቅ፤ ገንዘብ ወዳድነት፤ የዚህን አለም ክብር መናፈቅ እና የመሳሰሉት ናቸው። ለዚህ ችግር መፍትሔ ነው ብዬ ማስበው አስተምሮአችንን ማየትና ማጥራት እና ግልፅ የሆነ የልዩነት መስመር ማስመር ነው።"

ስለሰጠሽን ውድ ጊዜህ ተባረኪልን ሶሬቲ። በሌላ አልበም አና አገልግሎት እንድትባርኪን ጌታ ፀጋውን ያብዛልሽ።


@Zemareapp የምትከታተሉ ቤተሰቦቻችን ከሶሬቲ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደወደዳችሁት ባለ ሙሉ ተስፋ ነን።

በመጨረሻም 'እየራራህልኝ' ከተሰኘው የሶሬቲ መዝሙር በጣም የሚማርከንን ስንኝ እንጋብዛቹህ።
እየራራህልኝ ነው 3x
አንዴ ሳጠፋ ደሞ ሲደክመኝ
እየራራህልኝ ነው 3x
ብዙ በብዙ ስትምረኝ