ያልጠየቁት ዕድል
“ከገዢው ግቢ ሲወጡ ሳሉ ስምዖን የተባለውን የቀሬና አገር ሰው አገኙና የኢየሱስን መስቀል እንዲሸከም አስገደዱት።” ማቴዎስ 27፥32
የቀሬናው ስምዖን ይህንን ጊዜ በጭራሽ አልፈለገም። በፍቃዱ አልተነሳም፣ አላቀደም። እንዲሁ ከሕዝብ መካከል ተለይቶ የኢየሱስን ከባድ መስቀል እንዲሸከም ተደረገ። ከሩቅ ሲታይ፣ ድንገተኛና ፍትሐዊ ያልሆነ ይመስል ነበር። በጭራሽ ያልጠየቀው ሸክም ነበር።
ግን በእግዚአብሔር ዕቅድ ውስጥ፣ ድንገተኛ ዕድል የመሰለው ነገር እጣ ፈንታ ነበር። የስምዖን ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እስከ አሁን ይታወሳል። በኋላም በሐዋርያት ሥራ ውስጥ ከጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ጋር ተያይዞ ተጠቅሷል። ያልመረጠው ሸክም፣ እምነቱን የገለጸበት ቅጽበት ሆነ።
በዚያው ወቅት፣ ለዓመታት ከኢየሱስ ጋር የተመላለሱ ብዙዎች ፈርተው ተሰውረዋል። አብረውት የበሉና ተአምራቱን ያዩ ደቀ መዛሙርት ጠፍተው ነበር። ነገር ግን ይህ “ባዕድ” ሰው፣ በድንገት ወደ ታሪኩ ገብቶ፣ መስቀሉን ከኢየሱስ ጋር ተሸከመ።
ምን እንማራለን?
አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር ያልጠየቃችሁትን ዕድል ይሰጣችኃል። እንደ ሸክም ሳይሆን፣ እምነታችሁን የምታጠነክሩበት መንገድ አድርጋችሁ ተመልከቱት።
ታማኝነት ከቅርብነት ይበልጣል። ስምዖን መንገደኛ ሰው እንጂ የኢየሱስ የቅርብ ወዳጅ አልነበረም። ሆኖም እግዚአብሔር በታሪክ ውስጥ ልዩ ስፍራ ሰጠው።
ከአላማችን ስንቋረጥ ምናልባት ግብዣ ሊሆን ይችላል። እንደ ችግር ይምታዩት ነገር፣ ከኢየሱስ ጋር ወደተሻለ ግንኙነት የሚጠራችሁ ሊሆን ይችላል።
ይሄንን ለራሳችን እንጠይቅ
እግዚአብሔር እቅዴን ባልጠበቅኩት ወይም በከባድ ነገር ሲያቋርጠው፣ እሸሻለሁ ወይስ የኢየሱስን መስቀል ለመሸከም ወደ ዕድሉ እገባለሁ?
ጸሎት
ጌታ ሆይ፣ በፊቴ የምታስቀምጣቸውን ዕድሎች፣ ያልጠየቅኳቸውን እንኳን እንዳላሳልፍ እርዳኝ። መስቀሌን በእምነት ለመሸከም የሚያስችል ብርታት ስጠኝ፣ እና እያንዳንዱ መቋረጥ ወደ አንተ ለመቅረብ ግብዣ መሆኑን አስታውሰኝ። አሜን።