የእናንተ ምቾቶች ምንድን ናቸው?
አጋንንቱም ኢየሱስን፣ “የምታስወጣን ከሆነ ዐሣማዎቹ መንጋ ውስጥ እንድንገባ ፍቀድልን” ብለው ለመኑት። ኢየሱስም፣ “ሂዱ!” አላቸው። (ማቴዎስ 8:31)
ኢየሱስ እነዚያን አጋንንት ወዲያውኑ ለምን አላጠፋቸውም ብላችሁ አስባችሁ ታውቃላችሁ? ለምን ወደ አሳማዎቹ እንዲገቡ ፈቀደላቸው ከዚያም አሳማዎቹ ገደል ሲገቡ ዝም ብሎ ለምን ተመለከተ?
ነገሩ እንዲህ ነው፦ ኢየሱስ እዚያ ጋ አንድ ጥልቅ ነገር እያሳየን ነበር። ስለ እነዚያ የከተማ ሰዎች ብቻ ሳይሆን፣ ስለ እኛም ጭምር።
ያ ሰው ለዓመታት በአጋንንት እየተሠቃየ ነበር፤ በሁሉም ሰው የተገለለ፣ በራሱም ላይ ተስፋ የቆረጠ። በመጨረሻም ኢየሱስ ነፃ አወጣው። አስቡት እስኪ? ከዚህ ሁሉ መከራ በኋላ ነፃ ሲወጣ፣ ከተማው ሊደሰትለት፣ ሊያከብረው፣ ሊቀበለው ይችላል ብላችሁ ታስባላችሁ አይደል?
አይደለም። ይሉቁንም እነሱ ኢየሱስ ከከተማቸው እንዲሄድ ፈለጉ።
ለምን?
ምክንያቱም አሳማዎቻቸው በአይሁዳውያን ሕግ መሠረት ፍጹም ንጹሕ ያልሆኑ፣ መብላትም ሆነ መንካት የተከለከሉት እንስሳት ናቸው። ቢሆንም እንኳ፣ ለነርሱ የገንዘብ ምንጭ፣ ምቾት፣ እና ደህንነት የሰጧቸው እነዚያ ንብረቶች ድንገት ጠፍተዋል! የዚያ ሰው ነፃነት ከመጣው መከራ ይልቅ፣ የራሳቸው ንጹሕ ያልሆነ ኪሳራ የበለጠ አሳሰባቸው።
ይህ ታሪክ ከእናንተ ጋር የሚያመሳስለው ነገር አለ?
ስንት ጊዜ ነፃነትን፣ ለውጥን፣ ከጌታ ጋር አዲስ ህይወትን እንፈልጋለን። ግን ኢየሱስ የምንጣበቅባቸውን ነገሮች የእኛን ምቾቶች ማስወገድ ሲጀምር፣ ህይወታችንን ሲነካካ፣ እንፈራለን፣ እንጨነቃለን፣ ለምን ብለን እንጠይቃለን።
ለውጥ እንፈልጋለን፣ ግን ምንም ዋጋ የማያስከፍለን ከሆነ ብቻ። ኢየሱስ እንዲያድነን፣ እንዲለውጠን እንፈልጋለን፣ ግን ለተለምዶ ህይወታችን፣ ለምናውቀው ነገር፣ ለደህንነት ይሰማናል የምንለው ነገር ለማጣት እንፈራለን። ምንም እንኳን ያ ነገር ወደ ኋላ እየጎተተን ቢሆን። ምንም እንኳን ከእውነተኛው የኢየሱስ ህይወት እየከለከለን ቢሆን።
ኢየሱስ አጋንንቶቹ ወደ አሳማዎቹ እንዲገቡ የፈቀደው ዝም ብሎ አይደለም። የሰዎቹን ልብ ውስጥ ያለውን፣ ከነጻነታቸው በላይ የያዙትን ነገር፣ እንዲያውም ንጹሕ ያልሆነውንም ነገር ቢሆን እንኳን የያዙትን ነገር ለማሳየት ነበር።
ምናልባት አሁን በሕይወታችሁ ውስጥ አንዳንድ ነገሮች እንዲፈርሱ እየፈቀደ ያለው፣ ትኩረታችሁን ወዴት እንዳደረጋችሁ፣ በእውነት ምን እንደያዛችሁ ለማሳየት ሊሆን ይችላል። የእናንተን የልብ ቅድሚያ ለማሳየት
እናም ዛሬ ጥያቄው ይሄ ነው፦
የእናንተ ምቾቶች ምንድን ናቸው?
ኢየሱስ እንዲለውጣችሁ ከመፍቀድ ይልቅ፣ እርሱን ከህይወታችሁ ለማራቅ የምትፈሩት ምንድን ነው? ያንን ነገር ምን ያህል አጥብቃችሁ ይዛችሁታል?
አዎ፣ ከባድ ሊሆን ይችላል።
ግን፦ እውነተኛ ነፃነት ሁልጊዜ ዋጋ ያስከፍላል።
ለመልቀቅ ዝግጁ ናችሁ? ከልባችሁ መልቀቅ ትችላላችሁ?